የድኅነት መልካም ዜና
1የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን፥ ለታሰሩትም መፈታትን፥ ለዕውራንም ማየትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። 2የተወደደችውን የእግዚአብሔርንም ዓመት የተመረጠች ብዬ እጠራት ዘንድ፥ አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ፥ 3እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድም ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል። 4ከጥንት ጀምሮ የፈረሱትን ይሠራሉ፤ ከቀድሞ ጀምሮ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደ ገና ያድሳሉ። 5መጻተኞችም መጥተው በጎቻችሁን ይጠብቃሉ፥ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። 6እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፤ የአምላካችንም አገልጋዮች ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፤ በሀብታቸውም ትመካላችሁ። 7ሌላ ምድርን ይወርሳሉ፤ በራሳቸውም ዘለዓለማዊ ደስታ አላቸው። 8እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን የምወድድ፥ ስርቆትንና ቅሚያን የምጠላ ነኝ፤ እንደ ሥራቸውም ለጻድቃን እከፍላቸዋለሁ፤ ከእነርሱም ጋር የዘለዓለምን ቃል ኪዳን አደርጋለሁ። 9ዘራቸው በአሕዛብ መካከል፥ ልጆቻቸውም በወገኖች መካከል የታወቁ ይሆናሉ፤ ያያቸው ሁሉ እግዚአብሔር የባረካቸው ዘር እንደ ሆኑ ያውቃል፤ 10በእግዚአብሔርም እጅግ ደስ ይላቸዋል። ነፍሴም በእግዚአብሔር ሐሤት ታደርጋለች። ሽልማትን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማቷም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የደስታንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና። 11ምድርም ቡቃያውን እንደምታወጣ፥ ገነትም ዘሩን እንደሚያበቅል፥ እንዲሁ ጌታ እግዚአብሔር ጽድቅንና ደስታን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያበቅላል።