የሕዝቅያስ መታመምና መዳን
1በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል” አለው። 2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ 3“አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በቅን ልብ እንደ ሄድሁ፥ በፊትህም ደስ የሚያሰኝህን እንዳደረግሁ አስብ።” ሕዝቅያስም እጅግ ታላቅ ልቅሶን አለቀሰ። 4የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 5“ሂድ፤ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ 6አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ አድናለሁ፤ ለዚችም ከተማ እቆምላታለሁ። 7እግዚአብሔርም የተናገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል። 8እነሆ፥ በአባትህ የጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋራ የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።” ፀሐይም በጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ የወረደበት ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።
የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ጸሎት
9የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታምሞ ከደዌው በተፈወሰ ጊዜ የጸለየው ጸሎት ይህ ነው፦ 10እኔ እንዲህ አልሁ፥ “በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ ሲኦል በሮች እገባለሁ፤ 11ደግሞም፦ በሕያዋን ምድር የእግዚአብሔርን ማዳን፤ 12የቀረውንም ኑሬዬን አጣሁ። 13በዚያ ወራት እስኪነጋ ድረስ እንደ አንበሳ ታወክሁ፤ 14እንደ ሸመላ እንዲሁ ጮህሁ፤ 15ዐይኖች ደከሙ፤ ወደ ሰማይም ወደ እግዚአብሔር ማየት አልቻልሁም። 16ጌታ ሆይ፥ ስለ እርስዋ እንዲህ አልሁህ፤ ነፍሴን አዳንሃት፤ 17ሰውነቴንም እንዳትጠፋ ይቅር አልሃት፤ 18በመቃብር የሚኖሩ አያመሰግኑህምና፤ 19እኔ ዛሬ እንደማደርግ ሕያዋን ብቻ ያመሰግኑሃል፤ 20ጌታዬ ሆይ አንተ መድኀኒቴ ነህ፤ 21ኢሳይያስም ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፥ “የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተህ በእባጩ ላይ ለብጠው፤ አንተም ትፈወሳለህ።” 22ሕዝቅያስም፥ “ወደ እግዚአብሔር ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብሎ ነበር።