1በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኀጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። 2ወንጀላቸውን አንድ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው እንደ አሰቡ ክፋታቸውን ሁሉ ዐሰብሁ፤ አሁንም ክፋታቸው ከብባቸዋለች፤ በደላቸውም በፊቴ አለች። 3ነገሥታቱ በክፋታቸው፥ አለቆቹም በሐሰታቸው ደስ ተሰኙ። 4ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፤ ሁሉም እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቈያል። 5በንጉሦቻችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፤ እነርሱም ከዋዘኞች ጋር እጆቻቸውን ዘረጉ። 6እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፤ ጋጋሪያቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል። 7ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፤ ፈራጆቻቸውንም በሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፤ ከእነርሱም መካከል የሚጠራኝ የለም። 8ኤፍሬም ከሕዝቡ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው። 9ጠላት ጕልበቱን በላው፤ እርሱ ግን አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፤ እርሱም ገና አላስተዋለም። 10የእስራኤልም ውርደቱና ስድቡ በፊቱ ነው፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፤ በዚህም ሁሉ እግዚአብሔርን አልፈለጉትም። 11ኤፍሬምም ልብ እንደሌላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፤ ግብፅን ጠሩ፤ ወደ አሦርም ሄዱ። 12ሲሄዱም አሽክላዬን እዘረጋባቸዋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎችም አወርዳቸዋለሁ፤ መከራቸውን ሲሰሙ እገሥጻቸዋለሁ። 13ከእኔ ፈቀቅ ብለዋልና ወዮላቸው! እኔንም ስለ በደሉ ደንግጠዋል! እኔ ታደግኋቸው፤ እነርሱ ግን በሐሰት ተናገሩብኝ። 14በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ይገዳደሉ ነበር፤ 15በእኔም ዘንድ ተገሠጹ፤ እኔም ክንዳቸውን አጸናሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን መከሩብኝ። 16ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ሆኑ፤ አለቆቻቸውም ከምላሳቸው ስንፍና የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህም በግብፅ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።