ሆሴዕና አመንዝራዪቱ ሴት
1እግዚአብሔርም፥ “የእስራኤል ልጆች ወደ ሌሎች አማልክት ቢመለሱና የዘቢብ ጥፍጥፍን ቢወድዱ እንኳን፥ እግዚአብሔር እንደሚወድዳቸው አንተም ክፋትና ዝሙት ያለባትን ሴት ውደድ” አለኝ። 2እኔም በዐሥራ አምስት ብርና በአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ተኩል ገብስና በአንድ ፊቀን ወይን ተወዳጀኋት። 3“ከእኔ ጋር ብዙ ወራት ተቀመጪ፤ አታመንዝሪም፤ ሌላ ሰውንም አታግቢ፤ እኔም ከአንቺ ጋር እኖራለሁ” አልኋት። 4የእስራኤል ልጆች ያለ ንጉሥና ያለ አለቃ፥ ያለ መሥዋዕትና ያለ ምሥዋዕ፤ ያለ ካህንና ያለ ራእይ፤ ያለ ኤፉድና ያለ ተራፊም ብዙ ወራት ይቀመጣሉና፤ 5ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን እግዚአብሔርንና ቸርነቱን ያስቡታል።