ስለ ቀደመችው ድንኳን
1ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ሥርዐትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት። 2የመጀመሪያዪቱም ድንኳን ተዘጋጅታ ነበርና፥ በእርስዋም ቅድስት በምትባለው ውስጥ መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበረባት። 3ከሁለተኛው መጋረጃ በስተኋላ የነበረችውን የውስጠኛዪቱን ድንኳን ግን ቅድስተ ቅዱሳን ይሉአት ነበር። 4በውስጥዋም የወርቅ ማዕጠንትና ሁለንተናዋን በወርቅ የለበጡአት፥ የኪዳን ታቦት፥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የለመለመችው የአሮን በትር፥ የኪዳኑም ጽላት ነበሩባት። 5በላይዋም ማስተስረያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ነገር ግን በየመልኩ እናገረው ዘንድ ዛሬ ጊዜው አይደለም። 6ሥርዐቱ፥ ዝግጅቱም እንዲህ ነበር፤ በመጀመሪያዪቱም ድንኳን በየጊዜው አገልግሎታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ፥ ካህናት ዘወትር ይገቡ ነበር። 7ወደ ሁለተኛዪቱ ክፍል ግን ሊቀ ካህናቱ ኀጢአታቸውን ለማስተስረይ ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ የሚያቀርበውን ደም ይዞ፥ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻውን ይገባ ነበር። 8ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። 9ነገር ግን ለሚያቀርበው ሰው ግዳጅ መፈጸም የማይቻለውን መባና መሥዋዕት ያቀርቡበት የነበረው ለዚህ ዘመን ምሳሌ ሆነ። 10እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም፥ ስለ ልዩ ልዩ ጥምቀትም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዐቶች ብቻ ናቸው። 11ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ የሰው እጅ ወደ አልሠራት፥ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው፥ ከፊተኛዪቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን፥ 12የዘለዓለም መድኀኒትን ገንዘብ አድርጎ፥ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም። 13የላምና የፍየል ደም፥ በረከሱትም ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ፥ የሚያነጻና የረከሱትንም ሥጋቸውን የሚቀድሳቸው ከሆነ፥ 14ነውር የሌለው ሆኖ፥ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ይልቅ ያነጻ ይሆን? 15ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ፥ በቀደመው ሥርዐት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ፥ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ። 16ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡ ሰው ሞት ይመጣ ዘንድ ግድ ነው። 17የሙአች ሰው ኑዛዜ የጸናች ናት፤ ተናዛዡ በሕይወት ባለበት ጊዜ አትጠቅምምና። 18ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልከበረም። 19ሙሴ የኦሪትን ትእዛዝ ሁሉ ለመላው ሕዝብ ከነገረ በኋላ፥ የላምና የፍየል ደም ከውኃ ጋር ቀላቅሎ፥ ቀይ የበግ ጠጕርና የስሚዛ ቅጠል ነክሮ መጽሐፈ ኦሪቱንና ሕዝቡን ሁሉ ይረጭ ነበር። 20“እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው” ይላቸው ነበር። 21ድንኳኑንና የመገልገያውን ዕቃ ሁሉ በደሙ ይረጭ ነበር። 22ደግሞም በቀረበው ሁሉ እንዲህ ያደርግ ነበር፥ በኦሪት ሕግ ሁሉ በደም ይነጻ ነበር፤ ደም ሳይረጭ ግን አይሰረይም ነበር። 23በሰማይ ባለው አምሳል የተሠራው ይህ ሥራ፥ በዚህ ደም የሚነጻ ከሆነ፥ ይህ ሰማያዊ መሥዋዕትስ ከዚህ ይበልጣል። 24ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ፥ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። 25ሊቀ ካህናቱ ያደርገው እንደ ነበረ፥ በያመቱም ደም ይዞ ወደ ቅድስት ይገባ እንደ ነበረ ዘወትር ራሱን የሚሠዋ አይደለም። 26ይህስ ባይሆን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ በሞተ ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ፥ ራሱን በመሠዋት ኀጢአትን ይሽራት ዘንድ አንድ ጊዜ ተገለጠ። 27ለሰው አንድ ጊዜ ሞት፥ ከዚያም በኋላ ፍርድ እንደሚጠብቀው፥ 28እንዲሁ ክርስቶስም የብዙዎችን ኀጢአት ያስተሰርይ ዘንድ ራሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፤ በኋላ ግን ያድናቸው ዘንድ ተስፋ ለሚያደርጉት ያለ ኀጢአት ይገለጥላቸዋል።