ወደ ዕብራውያን 13
ስለ ፍቅርና እንግዳን ስለ መቀበል
1ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቅር ኑሩ። 2እንግዳ መቀበልንም አትርሱ፤ በዚህ ምክንያት ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ለመቀበል ያታደሉ አሉና። 3ከእነርሱ ጋር አብራችኋቸው እንደ ታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ ዐስቡ። 4መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፥ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለውም፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። 5ገንዘብ ሳትወዱ ኑሩ፤ ያላችሁም ይበቃችኋል፤ እርሱ “አልጥልህም፤ ቸልም አልልህም” ብሎአልና። 6አሁንም አምነን፥ “እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ አልፈራም፥ ሰው ምን ያደርገኛል?” እንበል። 7የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው። 8ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለም የሚኖር እርሱ ነውና። 9ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና። 10ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤ 11ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር። 12ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ። 13አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን፥ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ። 14በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም፤ የምትመጣውን እንሻለን እንጂ። 15በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? 16ነገር ግን ለድሆች መራራትን፥ ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።
መምህራንን ስለ ማክበር
17ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ ስለ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደ መሆናቸው፥ ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና። 18ይህም ስለ እኛ ትጸልዩ ዘንድ ይገባችኋል፤ ለሁሉ መልካም ነገርን እንደምትወዱና እንደምትሹ እናምናለን። 19ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ።
ቡራኬና ሰላምታ
20በዘለዓለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው፥ 21የሰላም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። 22ወንድሞች ሆይ፥ የምክርን ቃል እንድትቀበሉ እመክራችኋለሁ፤ በጥቂት ቃል ጽፌላችኋለሁና። 23ወንድማችን ጢሞቴዎስ ከእኛ ወደ እናንተ እንደ ተላከ ዕወቁ፤ ፈጥኖ ከመጣ አያችኋለሁ። 24መምህሮቻችሁን ሁሉና ቅዱሳንንም ሁሉ ሰላም በሉ፥ በኢጣልያ ያሉ ሁሉ ሰላም ብለዋችኋል። 25የጌታችን ጸጋዉ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።