ስለ አበው እምነት
1እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ፥ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት። 2በዚህም ለሽማግሌዎች ተመሰከረላቸው። 3ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠረ፥ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደ ሆነ በእምነት እናውቃለን። 4አቤል ከቃኤል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው። በዚህም ከሞተ በኋላ እንኳ ተናገረ። 5ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም፤ ሳይወሰድም እግዚአብሔርን ደስ እንደ አሰኘው ተመስክሮለታል። 6ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው አስቀድሞ እግዚአብሔር እንዳለ፥ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጣቸው ሊያምን ይገባዋል። 7ኖኅም ስለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ ፈራ፤ ቤተ ሰቡንም ያድን ዘንድ ክፍል ያላት መርከብን ሠራ፤ በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። 8አብርሃም በተጠራ ጊዜ ርስት አድርጎ ይወርሰው ዘንድ ወዳለው ሀገር ለመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚደርስም ሳያውቅ ሄደ። 9በእምነትም ከሀገሩ ወጥቶ ተስፋ በሰጠው ሀገር እንደ ስደተኛ በድንኳን፥ ተስፋውን ከሚወርሱአት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ኖረ። 10መሠረት ያላትን ሠሪዋና ፈጣሪዋ እግዚአብሔር የሆነላትን ከተማ ደጅ ይጠኑ ነበርና። 11ራስዋ ሳራም መካን ሳለች ባረጀችበት ወራት ዘር ታስገኝ ዘንድ በእምነት ኀይልን አገኘች፤ ተስፋ የሰጣት የታመነ እንደ ሆነ አምናለችና። 12ስለዚህም ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ፥ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ። 13እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፤ ተስፋቸውንም አላገኙም፤ ነገር ግን ከሩቅ አይተው እጅ ነሱኣት፤ በምድሪቱም ላይ እነርሱ እንግዶችና መጻተኞች እንደ ሆኑ ዐወቁ። 14እንዲህ የሚሉ ግን ሀገራቸውን እንደሚሹ ያሳያሉ። 15ከእርስዋ የወጡባትን ሀገር ቢሹ ኖሮስ፥ ወደ እርስዋ ሊመለሱ በተቻላቸው ነበር። 16አሁን ግን፥ በሰማያት ያለችውን የምትበልጠውን ሀገር ተስፋ ያደርጉ እንደ ነበር ታወቀ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ይጠራ ዘንድ በእነርሱ አያፍርም፤ ተስፋ ያደረጉአትን ሀገር አዘጋጅቶላቸዋልና። 17አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ በእምነት ወሰደው። 18“በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል” ብሎ ተስፋ ያናገረለትን አንድ ልጁን አቀረበው። 19እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኖአልና፤ ስለዚህም ያው የተሰጠው መታሰቢያ ሆነለት። 20ያገኙት ዘንድ ስለ አላቸው ነገር ይስሐቅ ያዕቆብንና ኤሳውን በእምነት ባረካቸው። 21ያዕቆብም በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩ ጫፍም ሰገደ። 22ዮሴፍም በሚሞትበት ጊዜ፥ ስለ እስራኤል ልጆች ከግብፅ መውጣት በእምነት ዐሰበ፤ ዐጽሙንም ትተው እንዳይወጡ አዘዘ። 23ሙሴ በተወለደ ጊዜ በእምነት ሦስት ወር በአባቱ ቤት ሸሸጉት፤ ሕፃኑ መልካም እንደ ሆነ አይተውታልና፤ የንጉሥንም ትእዛዝ አልፈሩም። 24ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ፤ 25ለጊዜው በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። 26የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሚሆን ዐውቆአልና፥ ዋጋውንም ተመልክቶአልና። 27የንጉሡንም ቍጣ ሳይፈራ፥ የግብፅን ሀገር በእምነት ተወ፤ ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ ወዶአልና። 28ቸነፈር በኵራቸውን እንዳያጠፋባቸው በእምነት ፋሲካን አደረገ፤ ደሙንም ረጨ። 29በደረቅ ምድር እንደ መሄድ የኤርትራን ባሕር በእምነት ተሻገሩአት፤ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ሰጠሙ። 30ሰባት ቀን ከዞሩአት በኋላ የኢያሪኮ ቅጽር በእምነት ወደቀ። 31ዘማ ረአብም በእምነት ከከሓዲዎች ጋር አልጠፋችም፤ ጕበኞችን በሰላም ተቀብላ ሰውራቸዋለችና። 32እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎን፥ ስለ ባርቅ፥ ስለ ሶምሶን፥ ስለ ዮፍታሔ፥ ስለ ዳዊት፥ ስለ ሳሙኤልና ስለ ሌሎች ነቢያት እነግራችሁ ዘንድ ጊዜዬ አጭር ነውና። 33እነርሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ ተስፋቸውን አገኙ፤ የአናብስትንም አፍ ዘጉ ። 34የእሳት ኀይልን አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ። 35ሴቶችም እንደ ትንሣኤ ቀን ተነሥተውላቸው ሙታኖቻቸውን ተቀበሉ፤ ተፈርዶባቸው የሞቱም አሉ፤ የምትበልጠውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ ሊድኑ አልወደዱምና። 36የገረፉአቸው፥ የዘበቱባቸውና ያሠሩአቸው ወደ ወህኒ ያገቡአቸውም አሉ። 37በመጋዝ የሰነጠቁአቸው፥ በድንጋይ የወገሩአቸው፥ በሰይፍም ስለት የገደሉዋቸው አሉ፤ ማቅ፥ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፥ ተጠሙም። 38ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፥ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ። 39እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙም። 40ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ስለ እኛ የምትበልጠውን አስቀድሞ በይኖአልና።