የእስራኤል ፍጻሜ መቃረብ
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፦ ፍጻሜ በእስራኤል ምድር ላይ መጣ፤ በምድሪቱ በአራቱም ማዕዘን ፍጻሜ መጣ። 3አሁንም ፍጻሜ በአንቺ ላይ ደርሶአል። ቍጣዬንም እሰድድብሻለሁ፤ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፤ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። 4ዐይኔም አይራራልሽም፤ እኔም ይቅር አልልሽም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ፤ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ነው፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” 5ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ክፋት በክፋት ላይ፤ እነሆ ይመጣል። 6ፍጻሜ መጥቶአል፤ ፍጻሜ መጥቶአል፤ ነቅቶብሻል፤ እነሆ ደርሶአል። 7በሀገር የምትኖር ሆይ! ስብራትህ ጊዜው ደረሰ፤ ቀኑም ቀረበ፤ የሽብር ቀን ነው እንጂ የተራራ ላይ ዕልልታ አይደለም፤ 8አሁን በቅርብ መዓቴን አፈስስብሻለሁ፤ ቍጣዬንም እፈጽምብሻለሁ፤ እንደመንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፤ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። 9ዐይኔም አይራራም፤ እኔም ይቅር አልልም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ፤ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ነው፤ እኔም እግዚአብሔር የምቀሥፍ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 10“እነሆ ቀኑ ደርሶአል፤ እነሆ! የእግዚአብሔር ቀን ወጥታለች፤ ስብራትህ ደርሶአል፤ ብትርም አብባለች፤ ስድብም በዝቶአል። 11የኀጢአተኛው ምርኩዝ ተሰበረ፤ በደል በዛች፤ ይኸውም በሁከት አይደለም፤ በችኮላም አይደለም። 12ጊዜው መጥቶአል፤ ቀኑ እነሆ ቀርቦአል፤ መቅሠፍቷ በሁለንተናዋ መልቶአልና የሚገዛ ደስ አይበለው፤ የሚሸጥም አይዘን። 13የገዛው ወደ ሻጩ አይመለስም፤ ዳግመኛም በሕይወት ይኖራል፤ ሁለንተናዋን አይቶአልና አልተመለሰም፤ የሰው ሕይወቱ በዐይኑ ፊት ነው። 14“መለከቱን ንፉ፤ ሁሉንም አዘጋጁ፤ ነገር ግን መዓቴ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና ወደ ሰልፍ የሚሄድ የለም። 15ሰይፍ በውጭ፥ ቸነፈርና ራብ በውስጥ አለ፤ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፤ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይፈጁታል። 16ከእነርሱም የሚሸሹ ይድናሉ፤ መብረርን እንደሚማር ርግብም በተራራ ላይ ይሆናሉ፤ እኔም በኀጢአታቸው ሁሉ እገድላለሁ። 17እጅ ሁሉ ትደክማለች፤ ጕልበትም ሁሉ እንደ ውኃ ይሆናል። 18ማቅም ትታጠቃላችሁ፤ ድንጋጤም ይሸፍናችኋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ ሐፍረት ይሆናል፤ በራሳችሁም ሁሉ ላይ ቡሃነት ይሆናል። 19ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም ይረክሳል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው አያድናቸውም። እርሱ የኀጢአታቸው እንቅፋት ሆኖአልና ሰውነታቸውን አያጠግቡም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉም። 20የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፤ የርኵስነታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አድርጌአታለሁ። 21በባዕድም እጅ ለንጥቂያ፥ በምድር ኀጢአተኞችም እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ያረክሱአቸዋል። 22ፊቴን ከእነርሱ እመልሳለሁ፤ ሥርዐቴንም ያረክሳሉ፤ ኀይለኞች ይገቡባታል፤ ያረክሱአትማል። 23“ምድር በአሕዛብ እንደ ተመላች፥ ከተማም በኀጢአት ተመልታለችና ሰንሰለት ሥራ። 24ከአሕዛብ ዘንድ ከሁሉ የሚከፉትን አመጣለሁ፤ ቤታቸውንም ይወርሳሉ፥ የኀያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፤ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ። 25ጥፋት መጥቶአል፤ ሰላምም ይሻሉ፤ እርሱም አይገኝም። 26ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል፤ ወዮታ በወዮታ ላይ ይከተላል፤ ከነቢዩም ዘንድ ራእይን ይሻሉ፤ ከካህኑም ዘንድ ሕግ፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል። 27ንጉሡም ያለቅሳል፥ አለቃም ውርደትን ይለብሳል፤ የምድርም ሕዝብ እጅ ትሰላለች፤ እንደ መንገዳቸውም መጠን አደርግባቸዋለሁ፤ በፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”