ትንቢተ ዳንኤል 3
ናቡከደነፆር ያቆመው የወርቅ ምስል
1ንጉሡ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ቁመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። 2ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹሞችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዢዎችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡ ናቡከደነፆርም ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ። 3በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹሞቹ፥ አዛዦቹና አዛውንቶቹ፥ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፥ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዢዎቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰበሰቡ፤ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ። 4አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ፥ “ሕዝብና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ! ንጉሥ ይላችኋል፥ 5የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፤ 6ወድቆም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።” 7ስለዚህ በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ ወገኖችና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ወድቀው፤ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ።
ሠለስቱ ደቂቅ
8በዚያን ጊዜ ከለዳውያን ቀርበው አይሁድን በንጉሡ በናቡከደነፆር ዘንድ ከሰሱ። 9እንዲህም አሉት፦“ንጉሥ ሆይ፥ ለዘለዓለም ኑር! 10ንጉሥ ሆይ! የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ሰው ሁሉ ወድቆ ለወርቁ ምስል ይስገድ፥ 11ወድቆም የማይሰግድ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ብለህ በቃልህ አዘህ ነበር። 12አሁንም ንጉሥ በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሾምኻቸው፥ ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዝህን እምቢ ያሉ፥ አምላክህን ያላመለኩ፥ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ ሚሳቅና ሲድራቅ፥ አብደናጎም የሚባሉ ሦስት ሰዎች አሉ።” 13ያንጊዜም ናቡከደነፆር ተቈጣ፤ በቍጣም ሲድራቅንና ሚሳቅን፥ አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፤ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። 14ናቡከደነፆርም፥ “ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? 15አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?” ብሎ ተናገራቸው። 16ሲድራቅና ሚሳቅ፥ አብደናጎም መለሱ፤ ንጉሡንም፥ “ናቡከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም። 17ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፥ ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ 18ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ” አሉት። 19የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ፥ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፤ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፤ እርሱም ተናገረ፤ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ። 20ሲድራቅንና ሚሳቅን፥ አብደናጎንም አስረው፥ ወደሚነድድ ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ ኃያላን ሰዎችን አዘዘ። 21የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ከሰናፊላቸውና ከጫማቸው፥ ከቀሚሳቸውና ከመጎናጸፊያቸውም፥ ከቀረውም ልብሳቸው ጋር አስረው በሚነድድ በእቶን እሳት ውስጥ ጣሉአቸው። 22የንጉሡም ትእዛዝ እጅግ ስለ በረታ፥ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፥ ሲድራቅንና ሚሳቅን፥ አብደናጎንም የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው። 23እነዚህም ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅና ሚሳቅ፥ አብደናጎም ታስረው በሚነድደው በእቶኑ እሳት መካከል ወደቁ።
ጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ
24በእሳት መካከልም ተመላለሱ እግዚአብሔርንም ፈጽመው አመሰገኑት። 25አዛርያም ቁሞ እንዲህ ብሎ ጸለየ፥ በእሳቱም መካከል ምስጋናን ጀመረ፦ 26“የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር፤ 27ባመጣህብን ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህና፤ ሥራህ ሁሉ የታመነ ነው፤ ሥርዐትህም ሁሉ የቀና ነው፤ 28ባደረግህብን ነገር ሁሉ ፍትሕ ርትዕ አደረግህ፤ 29የተውንህ እኛ በድለናል፤ ስተናልና 30መልካም ይሆንልን ዘንድ፥ 31ያመጣህብንንና ያደረግህብንን ሁሉ በእውነተኛ ፍርድህ አደረግህብን። 32ከአንተ ፈጽመው በራቁ ኀጢአተኞችና ወንጀለኞች በሚሆኑ በጠላቶቻችን እጅ ጣልኸን፤ 33አሁንም አፋችንን እንከፍት ዘንድ አገባባችን አይደለም 34ስለ ስምህ ብለህ ፈጽመህ አሳልፈህ አትስጠን። 35ይቅርታህንም አታርቅብን። 36ዘራቸውን እንደ ሰማይ ኮከብ፥ 37ስለ ኀጢአታችን በሀገሩ ሁሉ ዛሬ የተዋረድን ሆን። 38በዚህ ወራት አለቃ የለም፤ ነቢይም የለም፤ ንጉሥም የለም፤ 39በየዋህ ልቡና በቀና መንፈስ ተቀበልልን እንጂ፤ 40እንደ ጊደሮችና ላሞች፥ 41አሁንም በፍጹም ልቡናችን እንከተልሃለን፤ እንፈራሃለንም፤ 42አታሳፍረን፤ ነገር ግን እንደ ቸርነትህና እንደ ይቅርታህ ብዛት አድርግልን፥ 43በተአምራትህም አድነን፤ 44አገልጋዮችህን ስቃይ ያሳዩአቸው ሁሉ ይፈሩ፤ በቅሚአቸውም ሁሉ ይፈሩ፤ ኀይላቸውም ይድከም፤ 45አንተ እግዚአብሔር ብቻህ አምላክ፥ 46እነዚያም ብላቴናዎች በንጉሥ ዘንድ ነገር ሠርተው ማጣላታቸውን አልተዉም፤ በእሳቱም ድኝ አደሮማር፥ ቁልቋል፥ ቅንጭብ ጨመሩ። 47ነበልባሉም ከጕድጓዱ አርባ ዘጠኝ ክንድ ከፍ ከፍ አለ። 48እሳቱም እየተመላለሰ በከለዳውያን ምድጃ ጕድጓድ አጠገብ ያገኘውን ሁሉ ያቃጥል ነበር። 49የእግዚአብሔርም መልአክ ከአናንያና ከአዛርያ ከሚሳኤልም ጋር ወደሚነደው ወደ እሳቱ ምድጃ ወርዶ ከምድጃ ያለውን እሳት መታው፤ 50የእሳቱንም ነበልባል እንደ ቀዝቃዛ ነፋስ አደረገው፤ እነዚያንም ሰዎች እሳቱ ምንም አልነካቸውም፤ የራሳቸውንም ጠጕር አልለበለባቸውም፤ አላስጨነቃቸውምም። 51ያንጊዜም እነዚያ ሦስቱ ሰዎች ሁሉ በአንድ አፍ ፈጽመው አመሰገኑ፤ በእሳቱ ጕድጓድ ውስጥም እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ እንዲህም አሉ፦ 52የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን፤ 53የጌትነቱ ቅዱስ ስምም ይክበር ይመስገን፤ 54በምትመሰገንበት ቅዱስ ቦታ አንተ የከበርህ ነህ፤ 55በኪሩቤል ላይ ሆነህ ጥልቆችን የምታይ አንተ የከበርህ ነህ፤ 56በጌትነትህም ዙፋን አንተ የከበርህ ነህ፤ 57ከሰማዮች በላይ የተመሰገንህ ነህ፤ 58የጌታ ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 59ሰማዮች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 60የጌታ መላእክት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 61ከሰማዮች በላይ ያሉ ውኃዎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 62የጌታ ኀይላት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 63ፀሐይና ጨረቃ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 64የሰማይ ከዋክብት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 65ጠልና ዝናም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 66ነፋሳት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 67እሳትና ዋዕይ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 68መዓልትና ሌሊት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 69ጠልና ጤዛ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 70ብርድና ውርጭ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 71ብርሃንና ጨለማ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 72ደጋና ቈላ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 73በረድና ጕም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 74መብረቅና ደመና እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 75ምድር እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች፤ 76ተራሮችና ኮረብቶች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 77በምድር የሚበቅሉ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 78ጥልቆች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 79ባሕርና ፈሳሾች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 80አንበሪና በውኃ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 81በሰማይ የሚበርሩ ወፎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 82አራዊትና እንስሳት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 83የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 84እስራኤል እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 85የጌታ ካህናት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 86የጌታ ባሪያዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 87መንፈስና የጻድቃን ነፍሳት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 88አናንያና አዛርያ፥ ሚሳኤልም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ 89እግዚአብሔር ከሞትና ከሲኦል እጅ አድኖናልና፥ ከሚነድድም ከምድጃው እሳት አስጥሎናልና፥ ከነበልባሉም መካከል አውጥቶናልና፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም አመስግኑት፤ ቸር ነውና ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና። 90የአማልክትን አምላክ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁላችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ተገዙለት፤ አመስግኑትም፤ ቸርነቱ ለዘለዓለም ነውና። 91ንጉሡ ናቡከደነፆርም ሲያመሰግኑ ሰምቶ ተደነቀ፤ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም፥ “ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን?” ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፥ “ንጉሥ ሆይ! እውነት ነው” አሉት። 92ንጉሡም፥ “እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ፤ ምንም የነካቸው የለም፤ የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” አለ። 93የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ፥ “እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ፥ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ” ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅ፥ አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ። 94አለቆች፥ መሳፍንቱና ሹሞቹም፥ አዛዦቹና የንጉሡ ኃያላን ተሰብስበው እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልበላው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተነካ፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ በላያቸው እንዳልነበረ አዩ። 95ንጉሡም በፊታቸው ለእግዚአብሔር ሰገደ፥ ናቡከደነፆርም መልሶ እንዲህ አለ፦ መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ፥ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን፥ የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን፥ በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ፥ የአብደናጎም አምላክ ይመስገን። 96እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ፥ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ይቈረጣሉ፤ ቤታቸውም ይዘረፋል ብየ አዝዣለሁ አለ። 97የዚያን ጊዜም ንጉሡ፥ ሲድራቅን ሚሳቅንና አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ሾማቸው፤ ከፍ ከፍም አደረጋቸው፤ በግዛቱ ያሉ አይሁድንም ሁሉ አስገዛላቸው።