የእስራኤል ሕዝብ ከስሕተት አለመማር
4“ወደ ቤቴል ገብታችሁ ኀጢአትን ሠራችሁ፤ በጌልገላም ኀጢአትን አበዛችሁ፤ በየማለዳውም መሥዋዕታችሁን፥ በየሦስተኛውም ቀን ዐሥራታችሁን አቀረባችሁ፤ 5ሕጉን በውጭ አነበባችሁ፤ የታመነም አላችሁት፤ በፈቃዳችሁም የምታቀርቡትን አውጁና አውሩ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 6“በከተማችሁ ሁሉ ጥርስን ማጥረስን፥ በስፍራችሁም ሁሉ እንጀራን ማጣትን ሰጠኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም ይላል እግዚአብሔር። 7መከር ሳይደርስ ገና ከሦስት ወር በፊት ዝናብን ከለከልኋችሁ፤ በአንድም ከተማ ላይ አዘነብሁ፤ በሌላውም ከተማ ላይ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ በአንድ ወገን ዘነበ፤ ያልዘነበበትም ወገን ደረቀ። 8የሁለት ወይም የሦስት ከተሞች ሰዎች ወደ አንዲት ከተማ ውኃ ይጠጡ ዘንድ ሄዱ፤ ነገር ግን አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 9በአባርና በቸነፈር መታኋችሁ፤ አትክልታችሁ፥ ወይናችሁና በለሳችሁ፥ ወይራችሁም ከበጀ በኋላ ተምች በላው፤ ይህም ሆኖ እናንተ ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 10“በግብፅ እንደ ሆነው ሞትን ሰደድሁባችሁ፤ ጐበዛዝቶቻችሁን በሰይፍ ገደልሁ፤ ፈረሶቻችሁንም አስማረክሁ፤ በሰፈራችሁም እሳትን ሰድጄ አጠፋኋችሁ፤ በዚህም ሁሉ እናንተ ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 11ሰዶምንና ገሞራን አስቀድሜ እንደ ገለበጥኋቸው፥ እንዲሁ ገለበጥኋችሁ፤ እናንተም ከእሳት ውስጥ እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፤ በዚህም ወደ እኔ አልተመለሳችሁም” ይላል እግዚአብሔር። 12“ስለዚህ እስራኤል ሆይ! እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤ እስራኤልም ሆይ! እንደዚህ ስለማደርግብህ የአምላክህን ስም ለመጥራት ተዘጋጅ። 13እነሆ ነጐድጓድን የሚያጸና፥ ነፋስንም የፈጠረ፥ የመሢሕን ነገር ለሰው የሚነግር፥ ንጋትን ጭጋግ የሚያደርግ፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ፥ ስሙ ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።”