የሐዋርያት ሥራ 7
የእስጢፋኖስ ምስክርነት
1ሊቀ ካህናቱም፥ “በእውነት እንዲህ ብለሃልን?” አለው። 2እርሱም እንዲህ አለ፥ “ወንድሞቻችንና አባቶቻችን ሆይ፥ ስሙ፤ የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ወደ ካራንም ሳይመጣ ተገለጠለት። 3‘ካገርህ ውጣ፤ ከዘመዶችህም ተለይ፤ እኔም ወደማሳይህ ሀገር ና’ አለው። 4ከዚህም በኋላ ከከለዳውያን ሀገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ፤ ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ፥ ዛሬ እናንተ ወደ አላችሁባት ወደዚች ሀገር አመጣው። 5በውስጥዋም አንድ ጫማ ታህል ስንኳን ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን እርሱ ከእርሱም በኋላ ዘሩ ሊገዛት ልጅ ሳይኖረው ያንጊዜ እርስዋን ያወርሰው ዘንድ ተስፋ ሰጠው። 6እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ ‘ዘርህ በባዕድ ሀገር መጻተኞች ሆነው ይኖራሉ፤ አራት መቶ ዓመትም ባሮች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ መከራም ያጸኑባቸዋል። 7ደግሞም እግዚአብሔር አለ፤ ባሮች አድርገው በሚገዙአቸው ወገኖች እኔ እፈርድባቸዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ፤ በዚህም ሀገር ያመልኩኛል።’ 8የግዝረትንም ኪዳን ሰጠው፤ ከዚህም በኋላ ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛው ቀንም ገረዘው፤ እንዲሁ ይስሐቅም ያዕቆብን፥ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የቀደሙ አባቶችን ገረዙ።
ስለ ዮሴፍ
9“የቀደሙ አባቶችም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብፅ ሀገር ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበረ። 10ከመከራውም ሁሉ አዳነው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፤ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይ ቢትወደድ አድርጎ ሾመው። 11በግብፅና በከነዓን ሀገር ሁሉ ረኃብና ታላቅ ጭንቅ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉት አጡ። 12ያዕቆብም በግብፅ ሀገር እህል እንዳለ ሰማ፤ አባቶቻችንንም አስቀድሞ ላካቸው። 13ወደ ግብፅም እንደ ገና በተመለሱ ጊዜ ወንድሞቹ ዮሴፍን ዐወቁት፤ ፈርዖንም የዮሴፍን ዘመዶች ዐወቃቸው። 14ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ እንዲጠሩአቸው ላከ፤ ቍጥራቸውም ሰባ አምስት ነፍስ ነበር።
ያዕቆብ ወደ ግብፅ ስለ መውረዱ
15“ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ፥ እርሱም አባቶቻችንም ሞቱ። 16ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በገንዘቡ በገዛው መቃብር ቀበሩዋቸው። 17“እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን በደረሰ ጊዜ እስራኤል በዙ፤ የግብፅንም ሀገር መሉ። 18ይህም ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ እስከ ነገሠ ድረስ ነበር። 19እርሱም ወገኖቻችንን ተተንኵሎ አባቶቻችንን መከራ አጸናባቸው፤ ወንድ ልጅንም ሁሉ እንዲገድሉ አዘዘ።
ስለ ሙሴ
20“ያንጊዜም ሙሴ ተወለደ፤ በእግዚአብሔር ፊትም የተወደደ ሆነ፤ ለሦስት ወርም በአባቱ ቤት አሳደጉት። 21በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው፤ ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው። 22ሙሴም የግብፅን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በሚናገረውና በሚሠራውም ሁሉ ብርቱ ሆነ። 23“አርባ ዓመት ሲሞላውም ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኛቸው በልቡ ዐሰበ። 24አንድ ግብፃዊም ዕብራዊውን ሲበድለው አገኘና ለዚያ ለተበደለው ረድቶ ግብፃዊውን ገደለው በአሸዋም ቀበረው። 25እርሱም እግዚአብሔር በእጁ ድኅነትን እንደሚያደርግላቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። 26በማግሥቱም ከመካከላቸው ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኘ፤ ሊያስታርቃቸውም ወድዶ፦ ‘እናንተማ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ለምን ትጣላላችሁ?’ አላቸው። 27ያም ባልንጀራውን የሚበድለው ገፋው፤ እንዲህም አለው፦ ‘አንተን በእኛ ላይ ዳኛና ፈራጅ አድርጎ ማን ሾመህ? 28ወይስ ትናንትና ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትሻለህን?’ 29ስለዚህም ነገር ሙሴ ኮብልሎ በምድያም ሀገር ስደተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆችን ወለደ። 30“አርባ ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ በበረሃ በደብረ ሲና የእግዚአብሔር መልአክ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው። 31ሙሴም አይቶ በአየው ተደነቀ፤ ሊያስተውለውም ቀረበ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው። 32‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤’ ሙሴም ተንቀጠቀጠ፤ መረዳትም አልቻለም። 33እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ ‘ጫማህን ከእግርህ አውልቅ፤ የቆምህባት ምድር የተቀደሰች ናትና። 34በግብፅ ያሉትን የወገኖችን መከራ ማየትን አይቻለሁ፤ ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ፤ አሁንም ና ወደ ግብፅ ሀገር ልላክህ።’
ሙሴ ወደ ግብፅ ስለ መላኩ
35“በእኛ ላይ አለቃና ፈራጅ ማን አድርጎሃል? ብለው የካዱትን ያን ሙሴን በቍጥቋጦው መካከል በታየው በመልአኩ እጅ እርሱን መልእክተኛና አዳኝ አድርጎ እግዚአብሔር ላከው። 36እርሱም አርባ ዘመን በግብፅ ሀገርና በኤርትራ ባሕር፥ በበረሃም ተአምራትንና ድንቅ ሥራን እየሠራ አወጣቸው። 37ለእስራኤልም ልጆች፦ ‘እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋልና እርሱን ስሙት’ ያላቸው ይህ ሙሴ ነው። 38በምድረ በዳ በማኅበሩ መካከል የነበረ እርሱ ነው፤ በደብረ ሲና ከአነጋገረው መልአክና፤ ከአባቶቻችንም ጋር ለእኛ ሊሰጠን የሕይወትን ቃል የተቀበለ እርሱ ነው። 39አባቶቻችን ለእርሱ መታዘዝን እንቢ አሉ፤ ከዱትም፤ ልባቸውንም ወደ ግብፅ ሀገር መለሱ። 40አሮንንም፦ ‘በፊት በፊታችን የሚሄዱ አማልክትን ሥራልን፤ ያ ከምድረ ግብፅ ያወጣን ሙሴ የሆነውን አናውቅምና’ አሉት። 41ያንጊዜም የጥጃ ምስል ሠሩ፤ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸው ሥራም ደስ አላቸው። 42እግዚአብሔርም ተለያቸው፤ የሰማይ ጭፍራን ያመልኩም ዘንድ ተዋቸው፤ የነቢያት መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ፤ ‘እናንት የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ በውኑ በምድረ በዳ ሳላችሁ አርባ ዐመት ያቀረባችሁልኝ ቍርባንና መሥዋዕት አለን? 43ነገር ግን የሞሎህን ድንኳን አነሣችሁ፤ ሬፋን የሚባለውንም ኮከብ አመለካችሁ፤ ትሰግዱላቸውም ዘንድ ምስሎቻቸውን አበጃችሁ፤ እኔም ወደ ባቢሎን እንድትማረኩ አደርጋችኋለሁ።’ 44“ሙሴን ተናግሮ እንደ አዘዘው በአሳየው ምሳሌ የሠራት የምስክር ድንኳን በአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች። 45ኢያሱና አባቶቻችንም በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ፊት አስወጥቶ ወደ ሰደዳቸው ወደ አሕዛብ ሀገር ከእነርሱ ጋር አገቡአት፤ እስከ ዳዊት ዘመንም ነበረች። 46ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ባለመዋልነትን አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ያገኝ ዘንድ ለመነ። 47ሰሎሞን ግን ቤትን ሠራለት። 48ነገር ግን ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት የሚኖር አይደለም፤ ነቢይ እንዲህ ብሎአልና። 49እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? የማርፍበት ቦታስ ምን ዐይነት ቦታ ነው? 50ይህን ሁሉ እጆች የሠሩት አይደለምን?’
ስለ እስጢፋኖስ የመጨረሻ ንግግር
51“እናንተ አንገታችሁ የደነደነ፥ ልባችሁም የተደፈነ፥ ጆሮአችሁም የደነቈረ፥ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ዘወትር ትቃወማላችሁ። 52አባቶቻችሁ ከነቢያት ያላሳደዱት ማን አለ? ዛሬም እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና የገደላችሁትን የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሉአቸው። 53በመላእክትም ሥርዐት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁትም።”
የእስጢፋኖስ በድንጋይ መገደል
54ይህንም ሰምተው ተበሳጩ፤ ልባቸውም ተናደደ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። 55በእስጢፋኖስም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላ፤ ወደ ሰማይም ተመለከተ፤ የእግዚአብሔርን ክብር፥ ኢየሱስም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ። 56“እነሆ ሰማይ ተከፍቶ፤ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ። 57እነርሱም በታላቅ ቃል ጮኹ፤ ጆሮአቸውንም ደፈኑ፤ በአንድነትም ተነሥተው ከበቡት። 58ከከተማም ወደ ውጭ ጐትተው አውጥተው ወገሩት፤ የሚወግሩት ሰዎችም ልብሳቸውን ሳውል በሚባል ጐልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ። 59እስጢፋኖስም፥ “ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል” እያለ ሲጸልይ ይወግሩት ነበር። 60በጕልበቱም ተንበርክኮ፥ “አቤቱ፥ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ ሞተ፤ ሳውልም በእስጢፋኖስ ሞት ተባባሪ ነበር።