የሐዋርያት ሥራ 1
1ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያደርገውና ሊያስተምረው የጀመረውን ሥራ ሁሉ አስቀድሜ በመጽሐፍ ጽፌልሃለሁ። 2በመንፈስ ቅዱስ የመረጣቸው ሐዋርያትን አዝዞ እስከ ዐረገባት ቀን ድረስ ያለውን ጽፌልሃለሁ። 3ሕማማትን ከተቀበለ በኋላ ብዙ ተአምራት በማሳየት አርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየነገራቸውና እያስተማራቸው ሕያው ሆኖ ራሱንገለጠላቸው።
ስለ ተስፋና ስለ ጥምቀት።
4ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ፥ “ከእኔ የሰማችሁትን የአብን ተስፋ ጠብቁ” ብሎ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው። 5“ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን እስከ ቅርብ ቀን ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” አላቸው። 6እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ፥ “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት። 7እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም። 8ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፥ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮች ትሆኑኛላችሁ።”
ስለ ዕርገት
9ይህንም እየነገራቸው ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ተቀበለችው፤ እነርሱም ወደ እርሱ እያዩ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ከዐይናቸውም ተሰወረ። 10እነርሱም ወደ ሰማይ አተኵረው ሲመለከቱ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች ነጫጭ ልብስ ለብሰው በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው። 11እነርሱም፥ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየአያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፥ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል” አሏቸው። 12ከዚህም በኋላ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እርሱም ለኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። 13ወደ ማደሪያቸውም በደረሱ ጊዜ ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ ማቴዎስ፥ በርተሎሜዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ። 14እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከጌታችን ከኢየሱስ እናት ከማርያም፥ ከወንድሞቹም ጋር በአንድነት ለጸሎት ይተጉ ነበር።
ስለ ሐዋርያዊት ምርጫ
15ያንጊዜም ጴጥሮስ ተነሣና በወንድሞቹ መካከል ቆመ፤ መቶ ሃያ ያህል ሰዎችም በዚያ ሳሉ እንዲህ አላቸው። 16“እናንተ ሰዎች ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስሙ፤ ጌታችን ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባል። 17እርሱም ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበር፤ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበር። 18ከዚህም በኋላ ይህ ሰው በዐመፅ ዋጋዉ መሬት ገዛ፤ በምድር ላይም በግንባሩ ወደቀና ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ። 19በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ዜናዉ ተሰማ፤ ያም መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ ይኸውም የደም መሬት ማለት ነው። 20በመዝሙር መጽሐፍ ‘መኖሪያዉ ምድረ በዳ ትሁን፤ በውስጧም የሚኖር አይኑር፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ’ ተብሎ ተጽፎአልና። 21እንግዲህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ 22ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤዉ ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል።” 23ኢዮስጦስ የሚሉትን በርናባስ የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን ሰዎች አቆሙ። 24እንዲህም ብለው ጸለዩ፥ “አቤቱ፥ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ፥ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥኸውን አንዱን ግለጥ። 25ይሁዳ ወደ ሀገሩ ይሄድ ዘንድ የተዋትን ይህቺን የአገልግሎትና የሐዋርያነትን ቦታ የሚቀበላትን ግለጥ።” 26ዕጣም አጣጣሏቸው፤ ዕጣዉም በማትያስ ላይ ወጣ፤ ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋራም ተቈጠረ።