ዳዊት የሳኦልንና የዮናታንን ሞት እንደ ሰማ
1እንዲህም ሆነ፤ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመለሰ፤ ዳዊትም በሴቄላቅ ሁለት ቀን ተቀመጠ። 2በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሰፈር ከሳኦል ወገን አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ፥ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፤ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በምድር ላይ ወድቆ ሰገደለት። 3ዳዊትም፥ “ከወዴት መጣህ?” አለው፤ እርሱም፥ “ከእስራኤል ሰፈር አምልጬ መጣሁ” አለው። 4ዳዊትም፥ “ነገሩ ምንድን ነው? እስኪ ንገረኝ” አለው። እርሱም መልሶ፥ “ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፤ ከሕዝቡም ብዙው ወደቁ፤ ሞቱም፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ደግሞ ሞተዋል” አለው። 5ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ጐልማሳ፥ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ እንዴት ዐወቅህ?” አለው። 6ወሬውን ያመጣለት ጎልማሳም አለ፥ “በጌላቡሄ ተራራ ተዋግተው ወደቁ፤ እነሆም፥ ሳኦል በጦሩ ላይ ተኝቶ ነበር፤ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት። 7ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፤ እኔም፦ እነሆኝ አልሁ። 8እርሱም፦ አንተ ማን ነህ? አለኝ፤ እኔም አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት። 9እርሱም፦ ክፉ ጨለማ ይዞኛልና ደግሞ እስካሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያውት ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ። 10እኔም ከወደቀ በኋላ አለመዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ፥ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፤ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት።” 11ዳዊትም ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። 12በጦር ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፥ ለይሁዳም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። 13ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ጐልማሳ፥ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው፤ እርሱም፥ “እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰለት። 14ዳዊትም፥ “ትገድለው ዘንድ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጅህን ስትዘረጋ እንዴት አልፈራህም?” አለው። 15ዳዊትም ከብላቴኖቹ አንዱን ጠርቶ፥ “ሂድና ግደለው” አለው፤ ገደለውም። 16ዳዊትም፥ “እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው።