ስለ ደቀ መዛሙርት
1ወንድሞቻችን አሁን ደግሞ ራሳችንን እያመሰገን ልንነግራችሁ እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች ስለ እኛ ወደ እናንተ ደብዳቤ እንዲጽፉላችሁ፥ ወይስ እናንተ ትጽፉልን ዘንድ የምንሻው አለን? 2የእኛስ መጽሐፋችን እናንተ ናችሁ፤ በልባችን ውስጥም ተጽፋችኋል፤ ትታወቃላችሁም፤ ሰውም ሁሉ ያነብባችኋል። 3እናንተ ራሳችሁም በእኛ የተላከች የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ ያውቃሉ፤ ይህቺውም የተጻፈች በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ ነው እንጂ በቀለም አይደለም፤ በሥጋ ልብ ሠሌዳነት ነው እንጂ በድንጋይ ሠሌዳም አይደለም። 4ነገር ግን በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ ያለ እምነት አለን። 5ኀይላችን ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ ከእኛ ከራሳችን እንደ ሆነ አድርገን ምንም ልናስብ አይገባንም። 6በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ሕግ አገልጋዮች አደረገን፤ ፊደል ይገድላል፥ መንፈስ ግን ሕያው ያደርጋል።
ስለ መልእክታት መበላለጥ
7ስለዚያ ስለ አለፈው የፊቱ ብርሃን የእስራኤል ልጆች የሙሴን ፊት መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ በዚያች በድንጋይ ላይ በፊደል ለተቀረጸች ለሞት መልእክት ክብር ከተደረገላት፥ 8ለመንፈስ ቅዱስ መልእክትማ ምንኛ እጅግ ክብር ሊደረግ ይገባ ይሆን? 9ኵነኔን ለምታመጣ መልእክት ብዙ ክብር ከተደረገላት የጽድቅ መልእክትማ ምን ያህል ትከብርና ትመሰገን ይሆን? 10በዚህ ፍጹም ክብር ባነጻጸሯት ጊዜ የከበረችው እንዳልከበረች ትሆናለችና። 11ያ የሚያልፈው ክብር ካገኘ፥ ያ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት እጅግ ክብር ያገኝ ይሆን? 12እንግዲህ ይህን ያህል ተስፋ ካለን በግልጥ ፊት ለፊት ልንቀርብ እንችላለን። 13የዚያን ይሻር የነበረውን መጨረሻ፥ የእስራኤል ልጆች እንዳያዩት ፊቱን ይሸፍን እንደ ነበረው እንደ ሙሴ አይደለም። 14ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ልባቸው ተሸፍኖአል፤ ያም መጋረጃ ብሉይ ኪዳን በተነበበት ዘመን ሁሉ ጸንቶ ኖሮአል፤ ክርስቶስ እስኪያሳልፈው ድረስ አልተገለጠምና። 15እስከ ዛሬም የሙሴን ሕግ ሲያነብቡ ያ መጋረጃ ልባቸውን ይሸፍናቸዋል። 16ወደ እግዚአብሔር በተመለሱ ጊዜ ግን ያ መጋረጃ ከእነርሱ ይርቃል። 17እግዚአብሔር መንፈስ ነውና፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ባለበትም በዚያ ነፃነት አለ። 18እኛስ ሁላችን ፊታችንን ገልጠን በመስተዋት እንደሚያይ የእግዚአብሔርን ክብር እናያለን፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ተሰጠን መጠን የእርሱን አርአያ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንገባለን።