የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ እንደ ገባ
1ሰሎሞንም አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፥ የመገልገያ ዕቃውንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነበረው ግምጃ ቤት አገባ። 2በዚያ ጊዜም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ፥ የእስራኤልንም ልጆች አባቶች ቤቶች መሳፍንት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 3የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ተሰበሰቡ። 4የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ሌዋውያንም ሁሉ ታቦቷን አነሡ። 5የምስክሩንም ድንኳን፥ በድንኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አወጡ፤ ታቦቷንም ካህናቱና ሌዋውያኑ አወጡ። 6ንጉሡም ሰሎሞንና የእስራኤል ማኅበር ሁሉ፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ በአንድነት በታቦቷ ፊት ሆነው ከብዛት የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። 7ካህናቱም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤትዋ አምጥተው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች በነበረው መቅደስ አኖሯት። 8ኪሩቤልም በታቦቷ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቷንና መሎጊያዎቹን በስተላዩ በኩል ይሸፍኑ ነበር። 9መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩና በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ ነገር ግን ከውጭ አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያ አሉ። 10በታቦቷም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላት በቀር ምንም አልነበረባትም። 11ከመቅደስም ከወጡ በኋላ በዚያ የነበሩት ካህናት ሁሉ ተቀድሰው ነበር፤ በሰሞናቸውም አልተከፈሉም ነበር። 12መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፥ ከአሳፍና ከኤማን፥ ከኤዶትምም ልጆች ጋር ወንድሞቻቸውም፥ ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና ከበሮ፥ መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ በኩል ቆመው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር መቶ ሃያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር። 13መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑ በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ፥ “እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ” እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመለከትና በጸናጽል፥ በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር የክብሩ ደመና የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። 14የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ መቆምና ማገልገል አልተቻላቸውም።