ንጉሡ ኢዮስያስ ለእግዚአብሔር የፋሲካን በዓል እንደ አከበረ
1ኢዮስያስም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ፋሲካ አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ አረዱ። 2ካህናቱንም በየሥርዐታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ አጸናቸው። 3በእስራኤልም ሁሉ መሥራት የሚችሉትን ሌዋውያን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያነጹና ቅድስቲቱንም ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ እንዲያኖሩ አዘዛቸው። ንጉሡም ኢዮስያስ አለ፥ “በትከሻችሁ የምትሸከሙት አንዳች ነገር አይኑር፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ 4የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊት እንደ አዘዘ፥ ልጁም ሰሎሞን እንደ አዘዘ በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ተዘጋጁ፤ 5እንደ ሕዝቡም ልጆች እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶች ቤቶች አከፋፈል በመቅደሱ ቁሙ፤ እንዲሁም ለሌዋውያን በየአባቶቻቸው ቤት አከፋፈል ይሁን፤ 6የፋሲካውንም በግ እረዱ፤ እናንተም ተቀደሱ፥ እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የተናገረውን ቃል ታደርጉ ዘንድ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።” 7ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም ወይፈኖች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። 8አለቆቹም ለሕዝቡና ለካህናቱ፥ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የእግዚአብሔርም ቤት አለቆች፥ ኬልቅያስ፥ ዘካርያስ፥ ኢዮሔል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችንና ፍየሎችን፥ ሦስት መቶም በሬዎችን ለካህናቱ ሰጡ። 9የሌዋውያኑም አለቆች ኮኒንያስ በንያስም፥ ወንድሞቹም ሰማዕያስና ናትናኤል፥ ሰብንያስ፥ ኢዮሄል፥ ኢዮዛብድ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችን፥ አምስት መቶም በሬዎችን ለሌዋውያን ሰጡ። 10አገልግሎቱም ተዘጋጀ፤ ካህናቱም በየስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ። 11የፋሲካውንም በግ አረዱ፤ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም ቍርበቱን ገፈፉ። 12በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደ ክፍላቸው ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። 13የፋሲካውንም በግ እንደ ሙሴ ሥርዐት በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸትና በሰታቴ፥ በድስትም ቀቀሉ፤ ተከናወነላቸውም፤ ለሕዝቡም ልጆች ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። 14ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ከእነርሱ ጋር ላሉ ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለወንድሞቻቸው ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። 15የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሳፍም፥ እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደ ነበረው እንደ ኤዶትም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ በረኞቹም በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው ይርቁ ዘንድ አያስፈልጋቸውም ነበር። 16እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ፋሲካውንም ያደርጉ ዘንድ፥ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። 17የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣውን በዓል አደረጉ። 18ከነቢዩም ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልተደረገም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳደረጉት ያለ ፋሲካ ያደረገ የለም። 19ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ተደረገ። 20ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ካሰናዳ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የአሦርን ንጉሥ ይዋጋ ዘንድ ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ወጣ። 21እርሱም፥ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ እግዚአብሔርም እንድቸኩል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ተጠንቀቅ” ብሎ መልእክተኞችን ላከበት። 22ኢዮስያስ ግን ይዋጋው ዘንድ ተጽናና እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በእግዚአብሔርም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፤ በመጊዶንም ሸለቆ ይዋጋ ዘንድ መጣ። 23ቀስተኞቹም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም ብላቴኖቹን፥ “እጅግ ቈስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው። 24ብላቴኖቹም ከሰረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሰረገላ ውስጥ አስቀመጡት፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም በዚያ ሞተ፤ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። 25ኤርምያስም ለንጉሡ ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። 26የቀሩትም የኢዮስያስ ነገሮች፥ በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ 27የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል።