የይሁዳ ንጉሥ የምናሴ ዘመነ መንግሥት
1ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ። 2እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ። 3አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታ መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ ለበዓሊምም መሠዊያ ሠራ፤ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ተከለ፤ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም። 4እግዚአብሔርም፥ “ስሜ በኢየሩሳሌም ለዘለዓለም ይኖራል” ባለው በእግዚአብሔር ቤት የጣዖት መሠዊያዎችን ሠራ። 5በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ አደባባዮች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ። 6በሄኖምም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፤ አስማትም አደረገ። መተተኛም ነበረ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገርን አደረገ። 7እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፥ “በዚህ ቤትና ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለዓለም አኖራለሁ፤ 8ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ በሙሴ የተሰጠውን ሕግና ሥርዐት ፍርድንም ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም፥ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላርቅም” ባለበት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሠራውን ጣዖትና የተቀረጸውን ምስል አቆመ። 9ምናሴም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳተ። 10እግዚአብሔርም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ግን አልሰሙትም። 11ስለዚህም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር ያዙት፤ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ። 13የንጉሡ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴም ጸለየ እንዲህም አለ፦
የምናሴ ጸሎት
14“ዓለምን ሁሉ የምትገዛ፥ 15በቃልህ ትእዛዝ ባሕርን የገሠጽሃት፥ 16ይኸውም በተመሰገነው ስምህ ነው፤ 17ለክብርህ ከፍተኛነት ፍጻሜ የለውምና፥ 18በትእዛዝህ ለሚሆነው ይቅርታ ስፍር ቍጥር የለውም፤ 19አሁንም አቤቱ፥ የጻድቃን አምላካቸው አንተ ነህ። 20ቍጥሩ ከባሕር አሸዋ የሚበልጥ በደልን በድያለሁና፥ 21ከንቱውን ስመለከት የማይጠቅመኝንም ነገር ሳበዛ 22አሁንም ቸርነትህን እየለመንሁ በልቤ ጕልበት እሰግዳለሁ። 23አቤቱ፥ ጌታዬ፥ ፈጽሜ በደልሁ፤ 24አንተንም እማልዳለሁ፤ እለምንህማለሁ፤ 25ለዘለዓለም ክፋቴን አትመልከትብኝ፤ 26በየጊዜውና በሕይወቴ ዘመን ሁሉ አመሰግንሃለሁ። 27ከዚህ በኋላ በዳዊት ከተማ በስተውጭው ከግዮን ሰሜናዊ ምዕራብ በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሣ በር መግቢያ ድረስ ቅጥር ሠራ። እስከ ዖፌልም አዞረበት፤ እጅግም ከፍ አደረገው፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጭፍራ አለቆችን አኖረ። 28እንግዶችንም አማልክትና ጣዖታቱንም ከእግዚአብሔር ቤት አራቀ፤ የእግዚአብሔርም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማዪቱ በስተውጭ ጣላቸው። 29የእግዚአብሔርንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፤ የደኅነትንና የምስጋናንም መሥዋዕት ሠዋበት፤ የይሁዳም ሕዝብ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አዘዘ። 30ሕዝቡ ግን ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ፈጽመው ርቀው ገና በኮረብታዎች ላይ ይሠዉ ነበር፥ 31የምናሴም የቀሩት ነገሮች፥ ወደ አምላኩም የጸለየው ጸሎት፥ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት የነቢያት ቃል፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። 32ደግሞም ጸሎቱን፥ እግዚአብሔር እንደ ሰማው፥ ኀጢአቱና መተላለፉ ሁሉ፥ ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ኮረብታውን የሠራበት ዐፀዱንና የተቀረጹትንም ምስሎች የተከለበት ስፍራ፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ የታሪክ መጽሐፍ ተጽፈዋል። 33ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤቱም አትክልት ቦታ ቀበሩት፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 34አሞጽ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ። 35አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ አሞጽም አባቱ ምናሴ ለሠራቸው ለተቀረጹት ምስሎች ሁሉ ሠዋ፤ አመለካቸውም። 36አባቱም ምናሴ ሰውነቱን እንዳዋረደ በእግዚአብሔር ፊት ሰውነቱን አላዋረደም፤ ነገር ግን አሞጽ መተላለፉን እጅግ አበዛ። 37አገልጋዮቹም ተነሡበት፤ በቤቱም ገደሉት። 38የሀገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ የተነሡትን ሁሉ ገደሉ፤ የሀገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡ።