የአካዝያስ ዘመነ መንግሥት
1በኢየሩሳሌምም የነበሩት ታናሹን ልጁን አካዝያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። የመጣባቸው የዓረብና የአሊማዞን የሽፍቶች ጭፍራ የእርሱን ታላቆች ወንድሞች ገድለዋቸው ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ። 2አካዝያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ጎቶልያ የተባለች የዘንበሪ ልጅ ነበረች። 3እናቱም ክፉ እንዲያደርግ ትመክረው ነበርና እርሱ ደግሞ በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ። 4ከአባቱም ሞት በኋላ የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ያጠፉት ዘንድ መካሪዎች ነበሩትና። 5በምክራቸውም ሄደ፤ ከእስራኤልም ንጉሥ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለዓድ ሊዋጋ ሄደ፤ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት። 6ከሶርያም ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ፤ ታምሞም ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የአክዓብን ልጅ ኢዮራምን ያይ ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ወረደ። 7ወደ ኢዮራም በመምጣቱም የአካዝያስ ጥፋት ከእግዚአብሔር ሆነ፤ በመጣም ጊዜ ከኢዮራም ጋር እግዚአብሔር የአክዓብን ቤት ያጠፋ ዘንድ ወደ ቀባው ወደ ናሚሲ ልጅ ወደ ኢዩ ወጣ። 8ኢዩም የአክዓብን ቤት ይበቀል ዘንድ የይሁዳን መሳፍንትና አካዝያስን ያገለግሉ የነበሩትን የአካዝያስን ወንድሞች አግኝቶ ገደላቸው። 9አካዝያስንም ፈለገው፤ በሰማርያም እየታከመ ሳለ አገኙት፤ ወደ ኢዩም አመጡት፤ እርሱም ገደለው፦ እነርሱም፥ “በፍጹም ልብ እግዚአብሔርን የፈለገው የኢዮሣፍጥ ልጅ ነው” ብለው ቀበሩት። ከአካዝያስም ቤት ማንም መንግሥትን ይይዝ ዘንድ የሚችል አልነበረም።
የአካዝያስ እናት ጎቶልያ
10የአካዝያስም እናት ጎቶልያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የይሁዳን ቤተ መንግሥት ዘር ሁሉ አጠፋች። 11የንጉሡ ልጅ ዮሳቤት ግን ከተገደሉት ከንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሰርቃ ወሰደች፤ እርሱንና ሞግዚቱን በእልፍኝ ውስጥ አኖረቻቸው፤ የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት የካህኑ የዮዳሄ ሚስት ዮሳቤት ከጎቶልያ ፊት ሸሸገችው፤ እርስዋም አልገደለችውም። 12ከእርስዋም ጋር በእግዚአብሔር ቤት ተሸሽጎ ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ፤ ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች።