ሳሙኤል የእስራኤል መሪ ስለመሆኑ
3ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ፥ “በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና ምስሎቻቸውን ከመካከላችሁ አርቁ፤ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድናችኋል” ብሎ ተናገራቸው። 4የእስራኤልም ልጆች የበዓሊምን አማልክትና የአስጣሮትን ምስሎች አራቁ፤ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ። 5ሳሙኤልም፥ “እስራኤልን ሁሉ ወደ መሴፋ ሰብስቡ፤ ስለ እናንተም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ” አለ። 6እነርሱም ወደ መሴፋ ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት በምድር ላይ አፈሰሱ፤ በዚያም ቀን ጾሙ፤ በዚያም፥ “በእግዚአብሔር ፊት በድለናል” አሉ። ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በመሴፋ ፈረደ። 7ፍልስጥኤማውያንም የእስራኤል ልጆች ወደ መሴፋ እንደ ተሰበሰቡ በሰሙ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን አለቆች በእስራኤል ላይ ዘመቱ፤ የእስራኤልም ልጆች ሰምተው ከፍልስጥኤማውያን ፊት ፈሩ። 8የእስራኤልም ልጆች ሳሙኤልን፥ “ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ከመጮኽ ዝም አትበል። እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነናል” አሉት። 9ሳሙኤልም አንድ የበግ ጠቦት ወስዶ ለእግዚአብሔር ፈጽሞ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ከሕዝቡ ጋር አቀረበው፤ ሳሙኤልም ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው። 10ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሣርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ የነጐድጓድ ድምፅ አንጐደጐደ፤ ደነገጡም፤ በእስራኤልም ፊት ድል ተመቱ። 11የእስራኤልም ሰዎች ከመሴፋ ወጡ፤ ፍልስጥኤማውያንንም አሳደዱ፤ በቤኮር ታችም እስኪደርሱ ድረስ መቱአቸው። 12ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በመሴፋና በአሮጌው ከተማ መካከል አኖረው፤ ስሙንም፥ “እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል” ሲል “አቤንኤዜር” ብሎ ጠራው። እብነ ረድኤት ማለት ነው። 13እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንን አዋረዳቸው፤ ዳግመኛም ከዚያ ወዲያ ወደ እስራኤል ድንበር አልወጡም፤ በሳሙኤልም ዘመን ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች። 14ፍልስጥኤማውያንም ከአስቀሎና ጀምሮ እስከ፤ ጌት ድረስ ከእስራኤል ልጆች የወሰዱአቸው ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱ፤ እስራኤልም ድንበሩን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወሰዱ። በእስራኤልና በአሞራውያን መካከልም ሰላም ሆነ። 15ሳሙኤልም በዘመኑ ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 16በየዓመቱም ወደ ቤቴል፥ ወደ ጌልጌላና ወደ መሴፋ ይዞር ነበር፤ በእነዚያም በተቀደሱ ስፍራዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 17ቤቱም በዚያ ነበረና ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር፤ በዚያም በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።