ለጣዖት የተሠዋውን መብላት ስለማይገባ
1ለጣዖታት ስለሚሠዉ መሥዋዕቶች ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን እናውቃለን፤ ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። 2ዐወቅሁ የሚል ቢኖር፥ ሊያውቅ የሚገባውን ገና አላወቀም። 3እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን እርሱ በእርሱ ዘንድ በእውነት የታወቀ ነው። 4ለጣዖታት የተሠዋውን ስለመብላት ግን ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደሆነ፥ ከአንድ እግዚአብሔርም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 5አማልክት የሚሉአቸው ነገሮች አሉና፤ በሰማይም ቢሆን፥ በምድርም ቢሆን፥ ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች ቢኖሩ፥ 6ለእኛስ ሁሉ ከእርሱ የሆነ፥ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ እግዚአብሔር አብ አለን፤ ሁሉ በእርሱ የሆነ፥ እኛም በእርሱ የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም አለን። 7ነገር ግን ሁሉ የሚያውቀው አይደለም፤ እስከ ዛሬ በጣዖታት ልማድ፥ ለጣዖት የተሠዋውን የሚበሉ አሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለሆነ ይረክሳል። 8መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያደርሰንም፤ ብንበላም አይረባንም፤ ባንበላም አይጎዳንም። 9ነገር ግን እናንተን በማየት ሌላው እንዳይሰናከል ተጠንቀቁ። 10አንተ አማኙ በጣዖት ቤት በማዕድ ተቀምጠህ ያየህ ቢኖር ያ ልቡ ደካማ የሆነ ሰው ወዲያው ለጣዖት የተሠዋውን ደፍሮ ይበላል። 11ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለት ያ ደካማ ወንድም አንተን በማየት ይጎዳል። 12በባልንጀሮቻችሁ ላይ እንዲህ የምትበድሉ ከሆነ ደካማ ሕሊናቸውንም የምታቈስሉ ከሆነ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። 13ነገር ግን በመብል ምክንያት ወንድሜ የሚሰናከል ከሆነ ወንድሜን እንዳላሰናክል ለዘለዓለም ሥጋን አልበላም።