በእምነት ስለ አለመውደቅ
1ወንድሞቻችን ሆይ፥ አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ። 2ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው። 3ሁሉም ያን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ። 4ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ። 5እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሁሉም ደስ አላለውም፤ ብዙዎቹ በምድረ በዳ ወድቀዋልና። 6እነርሱ እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ ክፉ እንዳንመኝ እነርሱ ለእኛ ምሳሌ ሆኑልን። 7“አሕዛብ ተቀመጡ፤ ይበሉና ይጠጡም ጀመር፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንደ አመለኩ ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። 8ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ፥ በአንድ ቀንም ሃያ ሦስት ሺህ ሰዎች እንደ ወደቁ አንሴስን። 9ከእነርሱም አንዳንዶቹ እግዚአብሔርን እንደ ተፈታተኑት፥ ነዘር እባብም እንደ አጠፋቸው እግዚአብሔርን አንፈታተን። 10ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጐራጐሩበት፥ በመቅሠፍትም እንደጠፉ አናንጐራጕር። 11እነርሱን ያገኛቸው ይህ ሁሉ ነገር በኋላ ዘመን ለምንነሣው ለእኛ ትምህርትና ምክር ሊሆነን ምሳሌ ሆኖ ተጻፈ። 12አሁንም ያ ቆሜአለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13በሰው ላይ እንደሚደርሰው ያለ ፈተና ነው እንጂ ሌላ ፈተና አያገኛችሁም። በምትችሉት መከራ ነው እንጂ በማትችሉት መከራ ትፈተኑ ዘንድ ያልተዋችሁ እግዚአብሔር የተመሰገነ ነው፤ እርሱም ከፈተና ትድኑ ዘንድ በመከራ ጊዜ ይረዳችኋል።
ከጣዖታት ስለ መራቅ
14ወንድሞች! አሁንም ጣዖት ከማምለክ ሽሹ። 15ለዐዋቂዎች እንደሚነገር እነግራችኋለሁ፤ ትክክለኛውንም እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። 16ይህ የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር አንድ አይደለምን? የምንፈትተው ይህስ ኅብስት ከክርስቶስ ሥጋ ጋር አንድ አይደለምን? 17ኅብስቱ አንድ እንደ ሆነ እንዲሁ እኛም ብዙዎች ስንሆን አንድ አካል ነን፤ ሁላችን ከአንድ ኅብስት እንቀበላለንና። 18እስራኤል ዘሥጋን ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን ይበላሉ፤ ከመሠዊያውም ጋር አንድ ይሆኑ አልነበረምን? 19እንግዲህ ምን እንላለን? ለጣዖታት የሚሠዋ መሥዋዕት ከንቱ ነው፤ ጣዖቶቻቸውም ከንቱ ናቸው። 20አሕዛብም የሚሠዉ ለአጋንንት ነው እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም፤ ነገር ግን የአጋንንት ተባባሪዎች እንድትሆኑ አልፈቅድላችሁም። 21የእግዚአብሔርን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ አንድ አድርጋችሁ መጠጣት አትችሉም፤ የእግዚአብሔርን ማዕድና የአጋንንትንም ማዕድ በአንድነት ልትበሉ አትችሉም። 22እንግዲህ እግዚአብሔርን እናስቀናውን? በውኑ እኛ ከእርሱ እንበረታለን? 23ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። 24ለባልንጀራችሁ እንጂ ለራሳችሁ አታድሉ። 25ደግሞም በሥጋ ገበያ የሚሸጡትን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ። 26“ምድር በመላዋ የእግዚአብሔር ናትና።” 27ያላመነ ሰው ቢጠራችሁ፥ ልትሄዱም ብትወዱ ያቀረቡላችሁን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ። 28እንግዲህ “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ያላችሁ ቢኖር ግን፥ ስለ ነገራችሁና ባልንጀራችሁም የሚጠራጠር ስለሆነ አትብሉ። 29ነጻነታችሁን እንዳይነቅፉአት አስረድተዋችኋልና። 30በጸጋ ብበላ ግን በነገሩ ስለማመሰግን ለምን ይነቅፉኛል። 31ብትበሉም፥ ብትጠጡም የምታደርጉትን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። 32ለአይሁድም፥ ለአረማውያንም፥ ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ያለ ማሰናከል አርአያ ሁኑአቸው። 33እኔም ሁሉን በሁሉ ነገር ደስ እንዳሰኝ ይድኑ ዘንድ የብዙዎችን ተድላ እሻለሁ እንጂ የራሴን ተድላ የምሻ አይደለሁምና።